ሕወሃት እንደ ኳስ የሚጫወትባቸው የኦሮሞ ልሂቃን – አበበ ቤርሳሞ

ሁሉም ባይባሉ አብዛኞቹ አዲስ አበባ ያልተወለዱና ያላደጉ ሰዎች ያሉበት፣ የሚኒስተሮች ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ዙሪያ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለፓርላማው አስተላልፏል። አዋጁ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል መካከል ሊኖረው ስለሚገባ የኢኮኖሚ፣ የግብር፣ የልማት ግንኙነቶችን ባለፈ በከተማዋ አስተዳደር ጣልቃ ገብቶ ከተማዋ በምን መልኩ መተዳደር እንዳለባት ለመወሰን የሞከረበት ሁኔታ ነው ያለው። የከተማዋን የሥራ ቋንቋ፣  ስም፣ በከተማዋ ያሉ ቦታዎች መጠሪያዎችን እና የከተማዋ አስተዳደር ትምህርት ፖሊሲን በተመለከተ ለአዲስ አበባ ህዝብ ሌሎች በአዋጅ ሕግ ሊያወጡለት ማለት ነው።
በሕወሃት/ኢሕአዴግ የአዲስ አበባ ህዝብ መብትና ፍላጎት ተጠይቆ አያውቁም። አዲስ አበባ ከታሪካዊዋ የሸዋ ክፍለ ሃገር ወጥታ ኦሮሚያ ዉስጥ እንዳለች ተደርጎ ሲወሰድ፣ በሕዝቡ ፍላጎት ሳይሆን በሕዝቡ ላይ ተጭኖ ነው። አሁንም አዋጅ ብለው፣ ወለጋና አርሲ ካሉ  የኦሮሞ አክራሪዎች ጋር ያላቸውን ልዩነቶች ማጥበብ የፖለቲካ ትርፍ ስለሚያስገኝላቸው፣ የአዲስ አበባን ሕዝብን የመጫወቻ ጆከር አድርገው ሊቆምሩበት  ነው። አሁንም ሕዝብ ሳይፈለግ ሕግ እየደነገጉለት ነው።
ይህን በማድረጋቸውም በይፋ ሕወሃት/ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ራሷን በራሷ ማስተዳደር ትችላለች የሚለውን የሕግ መንግስት አንቀጽ ሰርዞታል። በዚህ መልኩም፣ ለጊዜው የዘመኑ ሰዎች በመሆናቸዉና ሃይል ስላላቸው የፈለጉትን ለማድረግ ቢችሉም በቋሚነት ግን  በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚወሰኑ ማናቸውም አይነት ዉሳኔዎች ተቀባይነት አይኖራቸው። መሰረዛቸው አይቀሬ ነው።
በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚወስነው የአዲስ አበብባ ህዝብ ነው።  አዲስ አበባ ሕዝቡ በዘር ሳይለያይ በሰላም በፍቅር የሚኖርባት ከተማ ናት። በአዲስ አበባ የፈረንሳይ (ሊሴ)፣ የጣሊያን፣ የጀርመን ..ትምህርት ቤቶች አሉ። የአረብኛም እንደዚሁ። በአፋን ኦሮሞ፣ በጉራጌኛ፣ በትግሪኛ ግለሰቦች ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱ ምንም ችግር የለውም። በመንግስት ደረጃም ይከፈት ከተባለም፣ የከተማ አስተዳደር አምኖበት ፣ በቂ ባጀት ካለው ማድረግ ይችላል።ትክክለኛና ሕጋዊ አሰራሩም ይሄ ነው። እንጂ ከአዲስ አበባ ጋር ምን ግንኙነት የሌላቸው ከነጆ ወይም አዲግራት የመጡ በአዲስ አበባ ላይ ሊወስኑ አይችሉም። ይሄ አንዱና ትልቅ ነጥብ ነው።
አፋን ኦሮሞን የሥራ ቋንቋ በማድረጉ አንጻር የሚኒስተሮች ምክር ቤት ያወጣው አዋጅ ምን ያህል ኢፍትሃዊነት የጎደለውና የዘር መድሎ የሚያደርግ እንደሆነ በግልጽ ያሳያበት ሁኔታ መኖሩ ደግሞ ሌላ የዚህን አዋጅ ትልቅ ግድፈት የሚያሳይ ነው። አዋጁ አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሲጠይቅ በከተማዋ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች  የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ ከመፈለግ እንደሆነ ያስቀምጣል። ከላይ እንደገለጽኩት አንደኛ ይሄንን መወሰን ያለበት የአዲስ አበባ ሕዝብ ነው።
ሁለተኛ በከተማዋ ያለው አብዛኛው አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ አማርኛም እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የሚናገር እንደመሆኑ፣ በከተማዋ አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ መሆኑ አላስፈላጊ ነው። አማርኛ የማይናገር ኦሮሞ በከተማዋ ዉስጥ 1 ወይም 2 % ብቻ ቢሆን ነው።
ሶስተኛ የአዲስ አበባ 10% ነዋሪ ለሆነው አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ አፋን ኦሮሞ የሥራ ይደረግ ሲባል ተመሳሳይ ቁጥጥር ያላቸው ሌሎች ማህበረሰቦችም እንዳሉ መረሳት የለበትም። ለምሳሌ የጉራጌኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ  ወደ 8.4% ነው። ጉራጌኛም ለምን የሥራ ቋንቋ ይደረግ አልተባለም ? ለኦሮሞዉና ለጉራጌው ለምን የተለያዩ መለኪያዎች ?
ኦህዴዶች፣ የኦሮሞ ብሄረተኞች መቱ፣ ነቀምቴ የመሳሰሉትን በልማት ከማሳደግ አዲስ አበባ ላይ ይሄን ያህል ሙግት ሲፈጥሩ፣ ሌሎች ላይ ጣቶቻቸውን ሲቀስሩ፣ በአይኖቻቸው ላይ ያለው ትልቅ ምሰሶ ለምን ማየት እንደተሳናቸው አልገባኝም። አፋን ኦሮሞ ተናጋሪው በአዲስ አበባ 10% ነው። ከአሥራ ዘጠኙ የኦሮሚያ ዞኖች በስምንቱ አማርኛ አንደኛ ቋንቋቸው የሆኑ ከ10% በላይ ናቸው። በአራቱ ከ20 % በላይ። በአዳማ አማርኛ ተናጋሪዎች 60% ናቸው። ታዲያ ለ10% አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ በአዲስ አበባ አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ ይደረግ እያሉ በኦሮሚያስ ለምን አማርኛ የሥራ ቋንቋ ማድረግ አልፈለጉም ? ለኦሮምኛ ተናጋሪዎችና ለአማርኛ ተናጋሪው ለምን የተለያዩ መለኪያዎች ይኖራሉ ?
እንግዲህ የሕወሃት/ኦህዴድ እና የኦሮሞ ብሄረተኞች ፖለቲካ ይሄ ነው።  ዘር ? ለአንዱ ሰጥቶ ለሌላ መንፈግ፣  አንዱን አንስቶ ሌላው ማውረድ፣ ሁሉንም እኩል በማየት አገርን በእክኩልነት ለማስደግ ከመሞከር፣ የዘር ልዩነት በመፍጠር በዜጎች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር ማድረግ።
ይህ አይነቱ አካሄድ አያዋጣም። በተለይይም የኦሮሞዉን ማህበረሰብ የሚጎዳ ነው የሚሆነው። ኦሮምኛ ተናጋሪው በአዲስ አበባ 10% ብቻ በሆነባት አዲስ አበባን የኦሮሞ ብቻ ማድረግ አይቻልም። እንኳን አዲስ አበባን፣ ላለፉት 25 አመታት በኦሮሚያ ትልቅ ጸረ-አማርኛ ዘመቻ ተደርጎም፣ በሃይል አፋን ኦሮሞ ብቻ  የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ታውጆም፣ እነ ናዝሬት፣ እነ ደብረ ዘይት፣ እነ ዝዋይ፣ እነ ሻሸመኔ  እንደዉም የበለጠ አማርኛ ተናጋሪ ከተማዎች ነው የሆኑት። ምክንያቱም ትልቁ የአገሪቷ ቀጣሪ የፌዴራል መንግስቱ ነው። የግል ቢዝነሶችና ሱቆች የሚሰሩት በአብዛኛው በአማርኛ ነው። የክልሉ አስተዳደር ብቻ አፋን ኦሮሞ ብቻ ፖሊሲ ቢዘረጋም የኢኮኖሚክ አቅም ስለሌለው ምን ማድረግ አልቻለም። አሁን ለምሳሌ በደብረ ዘይት ትልቁ መስሪያ ቤት አየር ሃይል ነው። በዚያ የተሰሩ ሆቴል ቤቶችና መዝናኛ ቤቶችም የሚሰሩት በአማርኛ ነው። ለምን ደንበኞቻቸው ከነጆና ከደደር የሚመጡ አይደለም፤ እንደ አዲስ አበባ ካሉ ቦታዎች እንጅ።
አፋን ኦሮሞ እንዲስፋፋና የኦሮሞ ጥቅም እንዲጠበቅ ከተፈለገ በኦሮሞ ብሄረተኞች ዘንድ የአስተሳሰብ ለዉጥ ያስፈለጋል። በግርግር ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እየተጋጩ ከሕወሃት ፍርፋሪ ለመለቃቀም ከሚሯሯጡ የኦሮሞው ጥያቄ ከሌላው ማህበረሰብ ጥያቄ ጋር በማጣጣም ፣ ከሌላው ጋር በመሆኑ ለሁሉም የሚበጅ ስርዓት መዘርጋቱ ላይ ቢሰሩ ነው የሚሻላቸው።
  1. አፋን ኦሮሞ የኦሮሞዎች ሳይሆን የኢትዮጵያ ቋንቋ መሆኑን መረዳት እንዲኖር መስራት አለባቸው።
  2. የቁቤ ፊደልን ሌላው ማህበረሰብ አይቀበለውም። አፋን ኦሮሞ ፊደሉ በሳባ ፊደል እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል።
  3. የተወሰኑ የአፋር ኦሮሞ ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም ሳይሆን በሁሉም ተምህርት ቤቶች በአዲስ አበባና በሸዋ አፋን ኦሮሞ፣ ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ ጋር ትምህርት እንዲሰጥ መገፋፋት አለባቸው።
  4. አማርኛን መጥላት የላባቸው። በኦሮሚያ አማርኛም የሥራ ቋንቋ የመደረጉ ጥቅም በኦሮሚያ ያሉ አፋን ኦሮሞ የማይናገሩ ወገኖችን መብት ከማክበር አንጻር ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያም ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንዲስፋፋ ከማድረግ አንጻር ጥቅም እንዳለው መረዳት አለባቸው።
  5. በኦሮሚያ ያሉ ሌሎች ማህበረሰቦችን መብት ከኦሮሞው እኩል ማክበር አለባቸው።
ይሄን ማድረግ ካልቻሉ፣ የኦሮሞ ብሄረተኞች ተሸናፊ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው። አንደኛ አሁን የሚመጻደቁባት ኦሮሚያን እነርሱ ታግለው አይደለም ያመጡት። ሕወሃት አማራ ከሚባለው ጋር ሊከፋፍላቸው ስለፈለገ የቸራቸው እንጂ። አሁንም በሚኒስተሮች ምክር ቤት የረቀቀው አዋጅ በትግል ያመጡት አይደለም። የኦሮሞ ተቃዉሞን ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ሕወሃት በሃይል ጨፍልቆታል። ከዚህ በኋላ አንድም ቦታ ተቃዉሞ ማሰማት የሚቻልበት ሁኔታ አለ ብዬ አላስብም። ሆኖም ግን ሕወሃት በአማራው ክልል ተቃዉሞ ስለበረታበት፣ ማይኖሪቲ ሆኖ መግዛት ስለማይችል፣ አሁንም ክ25 አመታት በፎት የተጫወተዉን ጨዋታ ለመጫወት ስለፈለገ  ነው። የሚያሳዝነው ግን፣ ከዚህ በፊትም ሕወሃት እንደ ኳስ የጠለዛቸውን ረስተው አሁንም ለመጠለዝ የኦሮሞ ብሄረተኞች መዘጋጀታቸው ነው።
Share on Google Plus

About ethinews

    Blogger Comment
    Facebook Comment

0 comments:

Post a Comment